Press Release

Shagar Masjid Destruction – Amharic

From Harari Alliance for Justice and Equality (H.A.J.E)
H.A.J.E’s Press Release:
Date: May 30, 2023

በቅርቡ በኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ዳርቻ: በኦሮሚያ ክፍለ ከተማ በሆነችው ሸገር ላይ በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች እና በመስኪዶቻቸው ላይ አሳዛኝ እና አሰቃቂ ድርጊቶች ተከስተዋል። በኦሮሚያ ክልል ሸገር ክፍለ ከተማ ከአዲስ አበባ አጎራባች ክልል ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሙስሊም መኖሪያ ቤቶች በክልሉ አስተዳደር ውሳኔ የነዋሪዎችን ደህንነት ሳይጠብቁ ፈርሰዋል። ይህን ተከትሎም ያለቅድመ ማስታወቂያ በወረዳው ህዝበ ሙስሊም የተገነቡ ከአስራ ዘጠኝ በላይ መስጂዶች ፈርሰዋል። እና በጥቂት ሳምንታት ውስጥ የሸገር ነዋሪ የሆኑ በርካታ ሙስሊሞች በብዙ አመታት የተገነቡ ትን ንብረቶቻቸውንና እንዲሁም መስኪዶቻቸውን አጥተዋል። የመስጂዶቹን የማፍረስ እቅድ በተጠናከረ ሁኔታ ሲጀመር የክልሉ የኦሮሚያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ከድርጊቱ እንዲቆጠብ የክልሉን መንግስት በተደጋጋሚ ቢጠይቅም ሆን ተብሎ ችላ ተብሎ መስጂዶቹ ወድሟል። ሙስሊም አማኞች በውስጥ ሆነው ሰላት ሲሰግዱ አንዳንድ መስጂዶች መውደማቸውን ለማወቅ ችለናል። በሺዎች የሚቆጠሩ የቁርኣን ኪታቦችን ጨምሮ ሌሎች የመስጊድ ንብረቶችም አብረው ወድመዋል:: ይህ ሁሉ የተደረገው መስጂዶቹ ያለፈቃድ የተገነቡ ናቸው በሚል ነው። የነዚህን መስጂዶች ውድመት ተከትሎ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝበ ሙስሊም በአገሪቱ ዋንኛው በአንዋር መስጂድ እና በአልኑር መስጂድ የተቃውሞ ሰልፍ ሲያደርግ በሚያሳዝን ሁኔታ ጥይት ተተኩሶባቸው እስካሁን ሶስት ግለሰቦች ህይወታቸውን አጥተዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት አምስት አስርት አመታት የተከሰቱ እጅግ በጣም ብዙ አሰቃቂ እና ለማመን የሚከብዱ ክስተቶች ስለነበሩ ከዚህ የከፋ መጠበቅ የተለመደ ሆኗል። የክልሉ የኦሮሚያ እስልምና ምክር ቤትም ሆነ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ባለፉት ሳምንታት በተከሰቱት ጉዳዮች ላይ ቁርጠኛ አቋም የያዙ ሲሆን በሙስሊም ኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሰ ያለውን ጥፋት እንዴት ማስተካከል እንደሚቻል በማያሻማ መልኩ ገልጸዋል። እኛ የሐረሪ ትብብር ለፍትሕና እኩልነት በወቅታዊው ግፍና በደል ላይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የወሰደውን አቋም በጥብቅ የምንደግፍ ሲሆን የፌዴራል መንግስት ሁኔታውን በመቆጣጠር የሚከተሉትን እርምጃዎች በመውሰድ አፋጣኝ እልባት እንዲያገኝ እንጠይቃለን።

1.    የፌደራል መንግስት ባስቸኳይ ገንዘብ መድቦ የፈረሱትን መስጂዶች መልሶ ማቋቋም አለበት። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ እልፍ አእላፍ ችግሮች እየገጠሟት ስለሆነ መንግሥት እዚህም እዚያም አዳዲስና ሆን ተብሎ የታቀዱ ችግሮች ሲፈጠሩ ዝም ብሎ ማየት የለበትም። በኢትዮጵያ እስላማዊ ማህበረሰብ ውስጥ ብስጭትና ንዴቱ እየተባባሰና እየገነፈለ ነውና ይህን በቁጥጥር ስር ለማዋል አፋጣኝ መፍትሄዎች መወሰድ አለባቸው። መንግስት ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ህዝብ ያቀፈውን የሙስሊሞችን ስሜት ችላ እንዳይል መጠንቀቅ አለበት።

2.    ይህን ግፍ በመቃወም ለሞቱት ሙስሊም ቤተሰቦች የፌደራል መንግስት ተገቢውን ካሳ መክፈል አለበት።

3.    የፌደራሉ መንግስት የዜጎችን በሰላም የመኖር እና የእኩልነት መብቶቻቸውን የመጠቀም ዋስትና በማረጋገጥ የኢትዮጵያን ህገ መንግስት መንፈስና ህግ ለማስከበር ጠንካራ እርምጃ መውሰድ አለበት። በጉራጌ ዞን 1500 የሚደርሱ ሴት ተማሪዎች ሂጃብ ካላወለቃቹህ ተብለው (የእምነቱ ግዴታ የሆነ) ከአንድ የመንግስት ትምህርት ቤት መባረራቸውን በሰነድ የተዘገበ ሪፖርት አለ።

4.    ቤቶቻቸው የፈረሱባቸው የሸገር ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ቤታቸውን ለመስራት ገንዘባቸውን በማሰባሰብ ለብዙ አመታት ሲሰሩ ህይወታቸውን አሳልፈዋል ። ምንም እንኳን በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የሚቀርበው ሰበብ ነዋሪዎቹ ፍቃድ ባለማግኘታቸው ቢሆንም ብዙዎቹ ንብረቶች የተገነቡት ከባለስልጣኑ ተገቢውን ፍቃድ  አግኝተው እንደነበር ታውቆኣል። ስለሆነም የፌደራል መንግስት ግንባር ቀደም በመሆን ተገቢውን ካሳ እንዲከፍልና ቤታቸውን እንዲገነቡ እና ሌሎች ወጪዎችን በመሸፈን የደረሰባቸውን ግፍ እንዲክስ እንጠይቃለን።

5.    ከመቶ አስር ሚሊዮን በላይ ከሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥራቸው ከግማሽ በላይ የሆኑት ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ላይ የደረሰው ግፍ በእዚህ ገጽ  መዘርዘር አይቻልም። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በአዋጅ የተቋቋመበት ዋና አላማ የህዝበ ሙስሊሙንና የመላው ኢትዮጵያውያንን መብት ለማስከበርና ለማስጠበቅ ነው። ብሔርና ሃይማኖት ሳይለይ በማንም ላይ የሚደርሰው ግፍ በሁሉም ላይ የሚደርስ ጉዳት ነው። በሸገር ክፍለ ከተማ በተከሰተው  አጸያፊ ተግባር የኦሮሚያ እስልምና ምክር ቤትም ሆነ የእስልምና ጉዳዪች ጠቅላይ ምክር ቤት ተደጋጋሚ ማሳሰቢያዎች በክልሉ አስተዳደር ችላ በመባሉ ለበርካቶች ህይወት ጥፋት ምክንያት ሆኖኣል ። የበርካታ ሙስሊሞችን ህይወት የሚነካ ማንኛውም የመንግስት እርምጃ ከእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጋር ትክክለኛ ምክክር እና የቅርብ የስራ ግንኙነት ሊኖረው ይገባል። ነገር ግን በተቃራኒው፣ መንግስት ጉዳዮቹን ለመፈጸም የሙስሊሞች ምክር ቤትን እንደ ተራ የመንደር ማህበር መውሰድ የለበትም ። የሐረሪ ትብብር ለፍትሕና እኩልነት የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በህገ መንግስቱ በተደነገገው ደንብ መሰረት ስራውን እንዲሰራ አጥብቆ ይጠይቃል::

በነዚህ ፈታኝ ጊዜያት ሁሉም ኢትዮጵያውያን በአንድነት በመቆም በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ላይ እየደረሰ ያለውን በደሎች በመቃወም እንዲታገሉ  የሐረሪ ትብብር ለፍትሕና እኩልነት ጥሪውን ያቀርባል። ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሓይላቸውን በአንድነት በመሰብሰብ  እነዚህን በደሎች ለማረምና ለእምነታቸው እና ለማንነታቸው እንዲታገሉ በአንድ ድምፅም እንዲናገሩ እንጠይቃለን።

#ሸገር #ኢትዮጵያ #በኢትዮጵያውያንሙስሊሞች  #Harar